በእኛ፡ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያት ዘንድ፡ ሥቃይና ችግር፥ ሰቆቃና ልቅሶ፡ ለምን ጸና?

ከዓለሙ ሕዝብ ተለይተን፡ ''ኢትዮጵያውያን''፡ የመባልን፡ አክሊለ-ጸጋንና ልብሰ-ተክህኖን፡ በፈቃዳችን ስለተቀዳጀንና ስስለተጐናጸፍን፥ ዘውዱንና በትረ-ሥልጣኑንም፡ በፈቃዳችን ስለደፋንና ስለጨበጥን፥ የጨዋነት (የኢትዮጵያዊነት)፡ ሃይማኖትንና ምግባር መታወቂያንም፡ ስለያዝንና ስላነገብን ብቻ! ፈተናውና መከራው፥ ሥቃዩና ችግሩ፥ ሰቆቃውና ልቅሶው፡ በእኛ፡ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያት ዘንድ፡ እንደሚጸናና እንደሚበረታ፡ ከቶውኑ አያጠያይቅም።

አማናዊው፡ የሕይወት ቃልም፡ ገና፡ በሥነ-ፍጥረት፡ እንዲህ ሲል ገልጾ፡ አስታውቆታል፦ ''በአንተና (በሰይጣን) በሴቲቱ (በድንግል ማርያም) መካከል፥ በዘርህና (በርኵሳት መናፍስቱና ዘሩን በሚረጭባቸው፡ ክፉዎች፡ የሰው ልጆችና አገልጋዮቹ) በዘርዋም (በኢየሱስ ክርስቶስ፥ በቃል ኪዳን ልጆቿ፡ ኢትዮጵያውያን) መካከል፡ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ (የማርያም ልጅ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ)፡ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም (ሰይጣን)፡ ሰኰናውን (ኢትዮጵያውያን ልጆቹንና ክርስትናን በመቀበል፡ ለኢትዮጵያዊነት ጸጋ የበቍትን፡ እያንዳንዱን፡ ሰብአዊ ፍጥረት [ኢትዮጵያውያን]) ትቀጠቅጣለህ''፥ ኋላም፡ በነቢዩ አንደበት፡ ''እግዚአብሔር ግን፡ ከዓለም አስቀድሞ፡ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል፡ መድኃኒትን አደረገ፤ አንተ፡ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ፡ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ፤ አንተም፡ የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው''፥ ደግሞም፡ በፍጻሜ ዘመን፡ ''ዘንዶውም፡ ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ፡ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት (ድንግል ማርያምን) አሳደዳት፤ ከእባቡም ፊት ርቃ፡ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ (ኢትዮጵያ) እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች (ጠባቂ መላእክት፡ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል) ተሰጣት፤ እባቡም፡ ሴቲቱ በወንዝ (በመከራ ማዕበል) እንድትወሰድ ሊያደርግ፡ ወንዝ የሚያህልን ውኃ፡ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፤ ምድሪቱም (ምድራዊት የኾነችው፡ ዘውዳዊት መንግሥቱ፡ ኢትዮጵያ)፡ ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም፡ አፍዋን ከፍታ ዘንዶው፡ ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው፤ ዘንዶውም፡ በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ፡ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት (ቅዱሳት ኪዳናት) የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን፡ ከዘርዋ የቀሩትን (ኢትዮጵያውያንን) ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ (በፀረ ማርያሙ፡ የከሃዲያን ልቦና) ላይ ቆመ'' እንደተባለው ማለት ነው፤ ነገር ግን፡ እኚሁ፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፡ አጽንተው በያዙትና ባነገቡት፡ በቅዱሱ ኪዳን በቀናችዪቱ፡ የኢትዮጵያዊነት የተዋሕዶ ሃይማኖታቸውና ምግባራቸው፡ ድል የሚነሡትና ምትሓታዊዉን ዓለም፡ ጠቅልሎ ከሚያሳልፈው፡ ታላቍ የመከራ ማዕበል፡ የሚድኑ መኾኑ ይታወቃል፤ ለዚህም፡ አማናዊው፡ የሕይወት ቃል፡ እንዴህ ሲል፡ ማረጋገጫውን አስታውቋል፦ ''የእግዚአብሔርም ማኅተም (ሕያዋን የኾኑት፡ ፯ቱ ቅዱሳት ኪዳናት) በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር፡ በምድር ያለውን፡ ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ፡ እንዳይጐዱ ተባለላቸው'' የሚለው ነው። (ኦሪ.ዘል. ፫፥ ፲፭፤ መዝ. ፸፬፥ ፲፪-፲፬፤ ራእ. ፱፥ ፬።)

ወደ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ይኽን ይጫኑት