ለታላቁ ቃለ ዓዋድ (የአዋጅ ቃል) ቀዳሚ መልእክት!

ለታላቁ ቃለ ዓዋድ
 (የአዋጅ ቃል)
 ቀዳሚ መልእክት!

ይድረስ፦
"ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት ነን!"
 ለምትሉ ወገኖች!
 እንዲሁም፡
 ለሰው ልጆች ኹሉ!

የእግዚአብሔር መንግሥት የኾነችው ኢትዮጵያ፡ ለታማኞች ልጆቿ ተገልጻ፥ እነርሱም እየኖርዋትና እያገለገሏት፡ እስከዛሬ፡ ለሰባት ሽህ አምስት መቶ ዓስር ዓመታት፡ በነጻነት ህልውናዋ ያለች፥ አኹንም፡ በእነርሱ ዘንድ፡ በዚያው በሕያው ነጻ አቋሟ የቀጠለች መኾኗ ይታወቃል።

ይህች፡ ስመ ጥሩዪቱና ገናናዪቱ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ከጥንት ከመሠረት፡ እጆቿን ወደእግዚአብሔር፡ ያለማቋረጥ ዘርግታ፡ ለሰው ዘርና ለፍጥረተ-ዓለሙ ኹሉ የማለደችው ናት፤ ምልጃዋም፡ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ፡ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን፡ አንድ ልጁን፡ ወደእርሷ ልኮ፡ በሰውነት ትወልደው ዘንድ ፈቃዱ የኾነላት፥ ራሷንም፡ ለአምላክ እናትነት ያበቃችው የመለኮት ሙሽራ ናት፤ በዚህ ሙሽርነቷም፡ የጠፋውን የሰውን ዘርና ፍጥረተ ዓለሙን ኹሉ፡ ከክፋት እና ከጥፋት፥ ከኃጢኣት እና ከሞት፡ ለዘለዓለሙ፡ በቤዛነቱ ሊያድን፡ ወደዚህ ዓለም የመጣውን፡ የእግዚአብሔርን ልጅ፡ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችው፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።

"በአሕዛብ ኹሉ ላይ ምስክር እንዲኾን፡ ይህ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ምሥራች፡ በዓለም ኹሉ ይሰበካል! በዚያን ጊዜ፡ መጨረሻው ይመጣል።" ባለው፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ቃል መሠረት፡ ይህችው ኢትዮጵያ፡ በቃልና በመጽሓፍ ብቻ ሳይኾን፡ በኅዋ ሰሌዳዎች ልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ሳይቀር፡ "ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት!" በሚለው ስሟና ማንነቷ፡ ለመላው ዓለሙ ኹሉ እየታወጀች መኾኗ፡ ይኸው፡ በይፋ በሚታየው ተጨባጭ እውነታ ተረጋግጦ ይነበባል።

ከዚህ የተነሣ፡ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ባላመነው፡ ሥጋዊ ዓለም ዘንድ ተገልጻ የምትሰፍንበት ጊዜ በመቃረቡ፡ ባጠቃላይ፡ እያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር፥ በተለይም፡ "ኢትዮጵያዊ፥ ኢትዮጵያዊት ነኝ!" የሚለው ወገን፡ ይህን፡ ግዙፍ የኾነ እውነታ፡ በማስተዋል ተመልክቶ፡ ለራሱ፡ ምድራዊና ሰማያዊ ደኅንነት ሲል፡ በቶሎ፡ የየግሉን ማንነትና ምንነት በማስተካከል፡ እየራሱን እንዲያዘጋጅ፡ አምላካዊው የማስጠንቀቂያ ጥሪ፡ ለሚመለከተው ኹሉ ለማድረስ፥ ለማስታወስና ለማሳሰብ ነው።

እንዳስተዋላችሁት፡ በዮሓንስ ራእይ ላይ፡ "፮-፷፮"፥ ወይም፡ "፮፻፷፮" የሚለው አኀዝ የተሰጠው "የጥፋት ርኵሰት" መታወቂያ ቍጥር፡ ፮ኛ ወር በኾነው፡ በየካቲት ወር፥ ፲፱፻፷፮ ዓመተ ምሕረት፡ በኢትዮጵያ፡ በገሃድ ከተገለጠ፡ እነሆ፡ አርባ ዓመታትን እያስቆጠረ ይገኛል፤ የዚህ የኢትዮጵያ ትውልድ ጽኑ መከራ፡ በዚህ ረዥም ጊዜ ውስጥ፡ ማብቃቱ ቀርቶ፡ እየረቀቀና እያየለ፥ እየደረጀና እየተንሠራፋ ከመኼድ በቀር፡ የመቀነስ፥ ወይም የመርገብ ምልክትን እንደማያሳይ፡ ይኸው፡ በይፋ የሚታይ ኾኗል። ለምን? ምክንያቱን፡ ሰነድ ውስጥ ይመልከቱት።

ጥያቄዎችና፡ መልስ ኾነው የተጠቃለሉት ዓበይት ቍም-ነገሮች
፩ኛ. ኢትዮጵያዊነት፡ የምንነታችንና የማንነታችን መታወቂያ ስለመኾኑ።
፪ኛ. የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት በኦሪታውያኑ እስራኤላዊነትና በግብፃውያኑ ኦርቶዶክሳዊነት የተካኼደበት ጥቃት።
፫ኛ. ኢትዮጵያዊው ምንነታችሁ፡ ለብቻው ምንድን ነው?
፬ኛ. ኢትዮጵያዊው ማንነታችሁ፡ ለብቻው ምንድን ነው?
፭ኛ. ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሚኖሩበት፡ የእግዚአብሔር ሥርዓት፡ ክህነትና መንግሥት፡ በተዋሕዶ፡ አንድ ናቸው።
፮ኛ. በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ሥርዓት፡ ኢትዮጵያዊውና ኢትዮጵያዊቷ፡ እያንዳንዳቸው፡ ምእመን፥ ካህን እና ነጋሢ ናቸው።

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከትለው ይቀጥሉ!...