ሴትነት፡ በቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት።

በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት
ኪዳናዊ ሕይወት፡
"ሴትነት"።

   በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ሃይማኖት መሠረትና ሥርዓት፡ ሴትነት፡ ከጾታ ልዩነት በስተቀር፡ ከወንድነት፡ በምንም አይለይም። በኪዳነ መልከ ጼዴቅ ምክንያት፡ በእኩልነትና በትክክለኛነት፡ ማለትም፡ በእግዚአብሔር ልጅነት፥ በክህነትና በነጋሢነት፡ ኹለቱም፡ በአንድ ዙፋን ላይ የተቀመጡ ናቸው።
    ይህ እውነታ፡ ጥንት፡ ወደአሉታዊ መልኩ የተለወጠበት ኹኔታ፡ በመጀመሪያዎቹ አዳምና ሔዋን የተከሠተ ሲኾን፥ ኋላ፡ በፍጻሜ ዘመን፡ ወደአዎንታዊ መልኩ በተመለሰ ጊዚ፡ በድንግል ማርያምና በኢየሱስ ክርስቶስ ታይቶ ተረጋግጧል።
    የዚህ እውነታ ዝክረ ነገር፡ በኪዳናዊው ኢትዮጵያዊ፡ በንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ፡ በተዘጋጁት መጻሕፍት ውስጥ፡ ዝርዝር መግለጫና ሰፊ ማብራሪያ፥ የጠለቀ ሓተታም ተሰጥቶበት ይነበባል።
    ራሷን፡ ለቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ያበቃች፥ ከዚህ የተነሣም፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ኢትዮጵያ ካህን (አገልጋይ) የኾነች፡ አንዲት ኪዳናዊት እኅታችን፡ ይህን ርእሰ ነገር በሚመለከት፡ በኹለቱ ጾታዎች ወገኖች መካከል፡ በአንድ ሌላ የኅዋ ሰሌዳ ላይ የተደረገ፡ የአስተያየት ልውውጥን አግኝታ፡ ይኸው መድበል፡ ለዚህ፡ ከፍተኛና አሳሳቢ ጉዳይ፡ የቍም ነገር አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘቧ፡ በበኩሏ አጠናቅራና አቀናብራ የላከችልን ቅጂ፡ ለአንባቢዎቻችን እንደሚጠቅም ስላመንንበት፡ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኮ ኾናችሁ ትመለከቱት ዘንድ፡ እነሆ፡ በዚችው የእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኮ አርትተንና አሥምረን፥ አከናውነንና አጽድቀን አቅርበንላችኋል!
+ + +