ቍጥር ፭/፳፻፮ ዓ. ም. ቃለ-ዐዋድ።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ስለአምልኳችን ያለን እውቀትና የአፈጻጸሙ ሥርዓት ትክክለኛ ስለመኾኑ በተመለከተ።

ስለሰንበትና ስለስግደት፥ ስለድንግል ማርያምና ስለቅዱሱ ኪዳን ተልእኮ፡
ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ በቅዱሱ ኪዳን፡ የኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖቷ መሠረት፡ አጽንታ ያኖረችው ምግባራዊ ሥርዓቷ፡ ምን እንደኾነ፡ በግልጽና በትክክል ሊታወቅ ይገባል።

ሰንበትን በሚመለከት፦
"ሰንበት"፡ ጥንትም፥ እስከዛሬና ዛሬም፥ ለዘለዓለምም፡ አንዲት ናት፤ ኹለት ሰንበታት የሉም። ያች አንዲቷ ሰንበት፦ በቀዳማዊው የፍጥረት ዘመን፡"እግዚአብሔርም፡ ሰባተኛዋን ቀን ባረካት፤ ቀደሳትም፤ የጀመረውን የመፍጠር ሥራውን ኹሉ ፈጽሞ፡ በእርሷ ዐርፎባታልና።" የተባለችው ናት፤

መካከለኛውም የሕግ ዘመን፡ "የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ፡ አስብ! በስድስቱ ቀኖች፡ ሥራህን ኹሉ፥ ግዳጅህንም ኹሉ አድርግ! ሰባተኛዋ ቀን ግን፡ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሰንበቱ ናትና፡ በእርሷ፡ አትሥራ! ምንም ዓይነት ተግባርን አታድርግ!" የተባለላት፡ እርሷው ናት፤

በፍጻሜውም የሕይወት ዘመን፡ "በሰንበት፡ ማድረግ የሚገባው፡ በጎ ነገርን ነውን? ወይስ፡ ክፉ ነገርን? ነፍስ ማዳን? ወይስ፡ መግደል?" ብሎ፡ ለተቃዋሚዎቹ ላቀረበላቸው ጥያቄ፡ መልስ ስላልሰጡት፡ ሕሙማንን በመፈወስ፡ በሰንበት፡ በጎ ማድረግና ማዳን እንደሚገባ፥ ደግሞም፡ "ሰንበትማ፡ ስለሰው ተፈጠረች እንጂ፡ ሰው፡ ስለሰንበት አልተፈጠረም። የማርያም ልጅ፡ የሰንበት፡ ጌታዋ ነው።" ብሎ በማብራራት፡ የተናገረላት ናት።

"በአጠቃላዩም፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ በመስቀል ላይ ኾኖ፡ "ተፈጸመ ኵሉ!" ማለትም፡ "እንግዴህ፡ ኹሉ አበቃ!" ብሎ፡ ነፍሱን፡ በሥልጣኑ፡ ከሥጋው ከለየ በኋላ፡ "አይሁድ ግን፡ መሽቷልና፡ 'እነዚህ አስከሬኖች፡ ስለሰንበት፡ በየተሰቀሉበት አይደሩ! የዚች ሰንበት ቀን፡ ታላቅ ናትና!' አሉ።"የተባለችው፡ ይህችው፡ አንዲቷ ሰንበት ናት። "(ዘፍጥ. ፪፥ ፫። ዘፀአ. ፳፥ ፰-፲፩። ማር. ፪፥ ፳፯-፳፰፤ ፫፥ ፫-፬። ዮሓ. ፲፱፥ ፴፩።)

እንግዴህ፡ ያች፡ "የሰንበት፡ ፈጣሪዋና ጌታዋ የኾነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ በሰውነቱ ሞቶ ሣለ፡ መለኮትን የተዋሓደ ሥጋውን፡ በመቃብር አሳድሮ ያረፈባት፥ ነጻነትንም ለማወጅ፡ በነፍሱ፡ ወደሲዖል ወርዶ ያሳለፋት፡ የሰሙነ ሕማማቷ ሰንበት፡ ይህችው አንዲቷ ሰንበት ናት።

በዚህ መሠረት፡ ይህችው፡ አንዲቷ ሰንበት፡ በአንድነቷ ጸንታ፡ በሕያውነትና በዘለዓለማዊነት ቀጠለች እንጂ፡ "ሰንበተ ክርስቲያን" የተባለች፡ ሌላ ኹለተኛ ሰንበትን አላስገኘችም። ጥንቱንም፡ ይህችኑ፡ አንዲቷን ሰንበት የፈጠረውና ኋላም፡ "የሰንበት ጌታዋ" የተባለው፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ይህችኑ፡ አንዲቷን ሰንበቱን፡ በትንሣኤው፡ ሕያውትና ዘለዓለማዊት አደረጋት እንጂ፡ ሌላ፡ ኹለተኛ ሰንበትን አልፈጠረም፤ አልሠራም። ይህ፡ ኹለት ሰንበታት እንዳሉ የሚያስመስለው ትምህርትና ሥርዓት፡ የሰዎች እንጂ፡ የእግዚአብሔር አለመኾኑ፡ በዚህ እውነታ፡ ተረጋግጦ ይታወቃል።

ጥያቄዎችና፡ መልስ ኾነው የተጠቃለሉት ዓበይት ቍም-ነገሮች
፩ኛ. ስግደትንና በሚመለከት።
፪ኛ. ድንግል ማርያምን በሚመለከት።
፫ኛ. የቅዱሱን ኪዳን ተልእኮ በሚመለከት።

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...