ቤተ ሕዝብ፤ ቤተ ምልክና እና ቤተ ክህነት ሲባል ምን ማለት ነው?

በኢትዮጵያ ሰፍና የምትኖረው የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ሦስት የአገልግሎት አካላዊ ዘርፎች አሏት። እነዚህም፦

፩ኛ. ቤተ ሕዝብ

፪ኛ. ቤተ ክህነት እና

፫ኛ. ቤተ ምልክና ይባላሉ።

ጉዳዩን አግዝፎ ለማስረዳት፡ በሰብአዊው ተፈጥሮ፡ ቋሚ የኾነችው የነፍስ አካል፡ ሥጋዊ አካልና መንፈሳዊ አካል እንዳሏት ኹሉ፡ የእግዚአብሔር በኾነችውም መንግሥት፡ ቤተ ሕዝቡ፡ እንደነፍስ፥  ቤተ ምልክናው እንደሥጋ፥ ቤተ ክህነቱም፡ እንደመንፈስ አካላት ኾነው ይመደባሉ።

እንግዲህ፡ ግንዱ አካል ለኾነው፡ ለቤተ ሕዝቡ ሥጋዊ ህልውና፡ የሚያስፈልጉትን የአስተዳደርና የአገልግሎት ተግባራት ለማበርከት፡ የኃላፊነት ዘርፍ፡ የቤተ ምልክናው ሲኾን፥ ለቤተ ሕዝቡ መንፈሳዊ ህልውና፡ የሚያስፈልጉትን ለማበርከት ደግሞ፡ የኃላፊነቱን ዘርፍ የያዘው፡ ቤተ ክህነቱ ነው ማለት ነው። ይህ መሠረታዊ እምነት፡ የኢትዮጵያ ህልውና ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፡ በተለይም ከክርስቶስ ልደት ወዲህ፡ መደበኛ ሥርዓት ኾኖ፡ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያውያን ኹሉ፡ የተመረጡበትንና የተቀቡበትን ወግ እየደነገገ ሲመራና ምንጊዜም ሲያስፈጽም ኖርዋል።

በምድራዊ ሥልጣኔ የተራመደው፡ ዘመናዊው ዓለም፡ “የመጨረሻው የሥነ መንግሥት ብቅዓት ነው” ብሎ በሚታመንበት ብሔራዊ የአስተዳደር ሥርዓቱ፡ “ሕግ አውጪ፥ ሕግ ፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ” የሚላቸው ሥስቱ ዘርፎች፡ ይህን መዋቅር የተከተሉ በመኾናቸው፡ የዛሬው የሰው ልጅ እየተጠቀመበት ያለው፡ ያገርና የመንግሥት አስተዳደር ፍልስፍና፡ ምንጩ፡ ማንና ከየት እንደኾነ፡ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፤ ይኽውም፡ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ መኾኑን ነው።

(ለተጨማሪ ማብራሪያ ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ! ከገጽ ፩፻፲ ጀምሮ ይመልከቱ)

ወደ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ይኽን ይጫኑት