የመደበኞቹ ሆህያት፡ ምሥጢራዊ ትርጓሜ ምንድን ነው?

፳፪ቱ ቅዳሚዎችና መደበኞች ሆህያት፡ ለየቅላቸው፡ በዚያው በግእዝ ባሕርያቸው፡ ስመ አምላክነት ያለው ምሥጢራዊ ትርጓሜ አላቸው። ይኸውም እንደሚከተለው ነው፦

አ፡ አሌፍ ይባላል። በግእዙ፡ አሌፍ ብሂል፡ አብ ፈጣሬ ኲሉ ዓልም ይሚለው ትርጉሙ፡ አሌፍ፡ ዓለሙን ኹሉ የፈጠረ፡ እግዚአብሔር አብ ማለት ነው።

በ፡ ቤት ይባላል። በግእዙ፡ ቤት ብሂል፡ ባዕል እግዚአብሔር የሚለው፡ ቤት፡ እግዚአብሔር፡ ኹሉን የሚሰጥ ባለጸጋ ማለት ነው።

ገ፡ ጋሜል ይባላል። በግእዙ፡ ጋሜል ብሂል፡ ግሩም እግዚአብሔር የሚለው፡ ጋሜል፡ እግዚአብሔር የሚያስፈራ አምላክ ማለት ነው።

ደ፡ ዳሌጥ ይባላል። በግእዙ ዳሌጥ ብሂል ድልው እግዚአብሔር የሚለው፡ ዳሌጥ፡ እግዚአብሔር፡ በኹሉ ዝግጁ ማለት ነው።

ሀ፡ ሄ ይባላል። በግእዙ፡ ሄ ብሂል፡ ህልው እግዚአብሔር የሚለው ሄ እግዚአብሔር፡ በኹሉ አድሮ የሚኖር ማለት ነው።

ወ፡ ዋው ይባላል። በግእዙ ዋው ብሂል፡ ዋህድ እግዚአብሔር የሚለው፡ ዋው እግዚአብሔር፡ በሥላሴ አንድነት የሚመለክ ማለት ነው።

ዘ፡ ዛይ፡ ይባላል። በግእዙ ዛይ ብሂል፡ ዝኩር እግዚአብሔር የሚለው፡ ዛይ፡ እግዚአብሔር፡ በፍጥረቱ ሲታሰብ የሚኖር ማለት ነው።

ሐ፡ ሔት ይባላል። በግእዙ፡ ሄ ብሂል፡ ሕያው እግዚአብሔር የሚለው፡ ሄ፡ እግዚአብሔር፡ ኅልፈት የሌለበት፡ ለዘለዓለም የሚኖር ማለት ነው።

ጠ፡ ጤት ይባላል። በግእዙ፡ ጤት ብሂል፡ ጠቢብ እግዚአብሔር የሚለው፡ ጤት፡ እግዚአብሔር፡ ጥበቡ የማይደረስበት ማለት ነው።

የ፡ ዮድ ይባላል። በግእዙ፡ ዮድ ብሂል፡ የማን እግዚአብሔር የሚለው፡ ዮድ፡ እግዚአብሔር የቀኝ እጅ ማለት ነው።

ከ፡ ካፍ ይባላል። በግእዙ፡ ካፍ ብሂል፡ ከሃሊ እግዚአብሔር የሚለው፡ ካፍ፡ እግዚአብሔር፡ ኹሉን ቻይ አምላክ ማለት ነው።

ለ፡ ላሜድ ይባላል። በግእዙ፡ ላሜድ ብሂል ልዑል እግዚአብሔር የሚለው፡ ላሜድ፡ እግዚአብሔር፡ ከኹሉ የላቀ ማለት ነው።

መ፡ "ሜም" ይባላል። በግእዙ፡ "ሜም ብሂል 'ምዑዝ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ሜም፡ 'እግዚአብሔር፡ መልካም ሽታ ያለው'" ማለት ነው።

ነ፡ "ኖን" ይባላል። በግእዙ፡ "ኖን ብሂል፡ 'ንጉሥ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ኖን፡ 'እግዚአብሔር፡ ነገሥታትን የሚሠይም፡ ዘለዓለማዊው ንጉሥ'" ማለት ነው።

ሠ፡ "ሣምኬት" ይባላል። በግእዙ፡ "ሣምኬት ብሂል፡ 'ሠፋኒ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ሣምኬት፡ 'እግዚአብሔር፡ በኹሉ ላይ የሠለጠነ ጌታ'" ማለት ነው።

ዐ፡ "ዔ" ይባላል። በግእዙ፡ "ዔ ብሂል: 'ዐቢይ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ዔ፡ 'እግዚአብሔር፡ ታላቅ አምላክ'" ማለት ነው።

ፈ፡ "ፌ" ይባላል። በግእዙ፡ "ፌ ብሂል፡ 'ፍቁር እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ፌ: 'እግዚአብሔር፡ የፍጥረቱ ወዳጅ አምላክ'" ማለት ነው።

ጸ፡ "ጻዴ" ይባላል። በግእዙ፡ "ጻዴ ብሂል፡ 'ጻድቅ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ጻዴ፡ 'እግዚአብሔር፡ እውነተኛ አምላክ'" ማለት ነው።

ቀ፡ "ቆፍ" ይባላል። በግእዙ፡ "ቆፍ ብሂል፡ 'ቅሩብ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ቆፍ፡ 'እግዚአብሔር፡ ለፍጥረቱ ቅርብ የኾነ አምላክ'" ማለት ነው።

ረ፡ "ሬስ" ይባላል። በግእዙ፡ "ሬስ ብሂል፡ 'ርኡስ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ሬስ፡ 'እግዚአብሔር፡ የፍጥረቱ ኹሉ ራስ'" ማለት ነው።

ሰ፡ "ሳን" ይባላል። በግእዙ፡ "ሳን ብሂል፡ 'ስቡሕ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ሳን፡ 'እግዚአብሔር፡ በፍጥረቱ ዘንድ ሊመሰገን የሚገባው አምላክ'" ማለት ነው።

ተ፡ "ታው" ይባላል። በግእዙ፡ "ታው ብሂል፡ 'ትጉህ እግዚአብሔር' የሚለው፡ "ታው፡ 'እግዚአብሔር፡ ፍጥረቱን፡ ዘወትር ተግቶ የሚጠብቅ ፈጣሪ'" ማለት ነው።