የኢትዮጵያ ልጆች፡ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት፡ የምስጋና ጸሎት።

አባታችንና እናታችን፥ እኅታችንና ወንድማችን፥ መንፈሳችንም፡ እግዚአብሔር ሆይ!

አቤቱ እንቀድስሃለን እናመሰግንሃለንም፤ አቤቱ እናወድስሃለን፤ እንታመንብሃለን፤ አቤቱ እናገንሃለንም፤ ለቅዱስ ስምህ እንታዘዛለን፣ እንሰግድልሃለን፤ ጕልበት ኹሉ፡ ለአንተ ይሰግዳል፤ አንደበትም ኹሉ፡ ወደአንተ ይጮሃል።

አንተ፡ የአማልክት አምላክ ነህ፤ የገዢዎች ገዢ ነህ፤ የንጉሦችም ንጉሥ ነህ። አንተ፡ የሥጋዊው ኹሉ፥ የነፍሳዊዉም ኹሉ ወገን ፈጣሪ ነህ።

ልጅህ እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ "እናንተ ስትጸልዩ፡

'የሰማዩ አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ!መንግሥትህ ትምጣ! ፈቃድህ በሰማይ እንደኾነ፡ በምድርም፡ እንዲሁ ይኹን! የየዕለቱን ምግባችንን፡ ስጠን ለዛሬ! ኃጢኣታችንንና በደላችንን፡ ይቅር በለን! እኛም የበደሉንን፡ ይቅር እንደምንል! አቤቱ ወደፈተና አታግባን! ከክፉው ኹሉ፡ አድነን እንጂ! መንግሥት፡ የአንተ ናትና፥ ኃይልና ምስጋናም፤ ለዘለዓለሙ።' በሉ!" ብሎ፡ ያስተማረንን ጸሎታችንን፡

በእርሱው ቤዛነት ተቀብለህ፡ ለነፍሳችንና ለሥጋችን፡ ቸርነትህን አበረከትህልን፤ ምሕረትህን አደረግህልን፤ ፍቅርህን ፈጸምህልን፤ ጸጋህንም ሰጠኸን። ስለዚህ፡ አኹን፡ እኛም፡ ስምህን እየጠራን፡ እናመሰግንሃለን።

በመዳናችን ምሥዋዕ፡ በእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም እና በሰላማችን የመስቀል ቤዛ፡ በእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ፡ በዓለሙ ኹሉ ወረደልን።

ስለዚህ፡ በሰማይ ብቻ ሳይኾን፡ ዛሬ በምድርም፡ የምትኖር ኾንህ።

ስምህ፡ በምድርም ተቀደሰ።

መንግሥትህም መጣችልን።

በሰማይ የኾነው ፈቃድህ፡ በምድርም፡ እንዲሁ ኾነ።

የዕለት እንጀራችንን ብቻ ሳይኾን፡ በዕድሜያችን ኹሉ፡ የሚያስፈልገንን ምግበ ሥጋ፡ በሥነ ፍጥረት አዘጋጀህልን።

ለዘለዓለም ሕያዋን የሚያደርገንን፥ መድኃኒትና ምግበ ነፍስ የኾነንንም፡ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም፡ ለዘወትር ሰጠኸን።

እርሱም፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፣ ከእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም የነሣው ነው።

በእርሱም፡ ኃጢኣታችንንና በደላችንን ኹሉ፡ ለመቼውም ጊዜ ደመሰስህ። ፈጽመህም ይቅር አልኸን።

እኛም፡ የበደሉንን ኹሉ፡ ይቅር እንድንል አስቻልኸን።

የአንተ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ለመኾን በበቃንበት፣ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት፡ ባቀዳጀኸን፡ የጥምቀት ልደታችን አከበርኸን።

የንስሓንም ጸጋ አደልኸን።

ከማናቸውም ፈተና አወጣኸን።

ከክፉው ኹሉ አዳንኸን።

የሓሰቱን አባት ዲያብሎስንም፡ ድል አደረግህ።

ሞትንም አስወገድህ።

ልዩ በኾነችው፡ በመጀመሪያዋ የመንፈስ ትንሣኤ ሕይወት እና በዘለዓለማዊቷ የሰንበት ዓለም ለመኖር አበቃኸን።

እግዚአብሔር ሆይ! መጠኑ፡ ሊነገር ስለማይቻለው ቸርነትህና ምሕረትህ፥ ፍቅርህና ጸጋህ፥ እንዲሁም፡ የሚያስፈልገንን ኹሉ፡ ሳንለምንህ ስለምትሰጠን፡ ዘወትር እናመሰግንሃለን።

"ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት"፡ ክፋትን፥ ኃጢኣትንና ሞትን፡ ፈጽማ አጥፍታ፡ ለግዙፉ ዓለም፡ በገሃድ የምትገለጥበትንና በይፋ የምትሰፍንበትን ጊዜ፡ እንደተስፋ ቃልህ እንጠብቃለን።

እርሷም፡ "ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች!" በተባለችው፡ በእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም ንግሥትነት እና "የይሁዳው ነገድ አንበሳ፡ ድል ነሣ!" በተባለው፡ በእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ ንጉሥነት የምትመራው፥ እኛም፡ ዛሬ የምንኖርባት፣ የምናገለግላትም፡ የእውነት መንግሥትህ ናት።

ኃይልና ምስጋና፥ መንግሥትም፡ የአንተ ናቸው፤ ዛሬም፣ ዘወትርም፤

ለዘለዓለሙ፤ አሜን።