ጽላት ምንድን ነው? ታቦትስ?

ከእግዚአብሔር፡ በእግዚአብሔር ጣቶች፡ የተጻፈባቸውና ኹለቱን ጽላት የያዘችው፡ለሙሴም የተሰጠችው፡ አሥሩን ቃላት የያዘችው ሰሌዳ ጽላት ይባላል። የእርሷ ማኅደር የኾነው ደግሞ ታቦት ይባላል። የመጀመሪያዎቹ አምስቱ፡ ከሃይማኖታዊ አምልኮ ጋር የተያያዙ ሲኾኑ፤ ነፍስ፡ ሃይማኖቷን የምትመሠርትባቸውና እውነተኛነቷን፡ ለራስዋና ለፈጣሪዋ አረጋግጣ የምታሳይባቸው ባሕርያት ናቸው። የኋለኞቹ አምስቱ ደግሞ ከሃይማኖታዊ ምግባር የተያያዙ ሲኾኑ፤ ነፍስ፡ በሥጋዋ አማካይነት፡ ሃይማኖታዊ ምግባዋን፡ ለሌሎች ፍጡራን አረጋግጣ የምታሳይባቸው የሥራ መግለጫዎች ናቸው።

ይኹን እንጂ፡ አሥሩን ቃላት የያዘችው ዘለዓለማዊት ሕግ፡ በእግዚአብሔር ጣቶች፡ በእውነትና በመንፈስ፡ የተጻፈችው፡ ገና አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ እንደኾነ መጥቀሱ፡ አስፈላጊ ይኾናል። የተጻፈችውም፡ በኦሪት ጊዜ      እንደኾነው፡ በድንጋይ ጽላት ላይ ሳይኾን፡ “ሕሊና” በተባለው፡ በረቂቁ ሰብአዊ የልብ ጽላት ላይ ነው! አመሠራረቷ እንዲህ እንደመኾኑ፡ የሃይማኖት አምልኮቷና የምግባር ሥርዓቷ እንዲሁ፡ በእውነትና በመንፈስ እንዲፈጸም፡ መለኮታዊ ባሕርይዋ ይጠይቃል። ኪዳነ ልቦና ያሰኛት ቅሉ፡ ይህ ነው!

ከአዳምና ሔዋን ጀምሮ፡ በሰዎች ልቦና ላይ በእውነትና በመንፈስ ተጽፋ የምትኖረውን ይህችን፡ አሥሩን ቃላት የያዘችውን ሕግ፡ ኢትዮጵያውያን፡ ጽላተ ሙሴ ወደኢትዮጵያ ከመምጣቷ፡ ገና ከረዥም ዘመን በፊት፡ አስቀድመው፡ በኪዳነ ልቦና ጠብቀውና አጽንተው፡ በእውነትና በመንፈስ እየፈጸሙት ኖረዋል። ይህም ይታወቅ ዘንድ፡ ጥንት፡ በሥነ ፍጥረት የተሠራችውንና ከአሥሩ ቃላት መካከል፡ አንዷ የኾነችውን፡ ሰባተኛዋን፡ የእግዚአብሔርን የሰንበት ቀን፡ ገና፡ በኪዳነ ልቡና ሣሉ ጀምረው፡ ሲያደርጉ እንደኖሩት ኹሉ፡ ዛሬም፡ በኪዳነ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ውስጥ በሚገኙበት፡ በአኹኑ የክርስትና ዘመናቸው እንኳ፡ እነርሱ ብቻ፡ “ቀዳሚት ሰንበት” ወይም “ቅዳሜ” ብለው በመሠየም፡ ሲያከብሯት ይታያል።

ኢትዮጵያውያን፡ ቀድሞ፡ በኪዳነ ልቦና፡ በሰብአዊ ልባቸው ውስጥ፡ በእግዚአብሔር ጣቶች ተጽፋ ያገኟትን፥ ኃላ፡ በኪዳነ ኦሪት፡ በድንጋዩ ጽላት ላይ ተቀርፃ ያዩዋትን፥ በመጨረሻም፡ በኪዳነ ምሕረት፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፡ መንፈሳዊ አካላቸውን ተዋሕዶ የተመሰጡባትን፡ ያችን፡ አሥሩን የእግዚአብሔር ቃላት የያዘችውን የሕይወት ሕግ፡ በእውነተኛውና በመንፈስ ቅዱስ አምልኳቸው ጠብቀው ኖረዋታል፤ ዛሬም፡ እየኖርዋት ነው፡ ወደፊትም፡ ለዘለዓለም ይኖርዋታል።

(ለተጨማሪ ማብራሪያ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት፡ አንደኛ መጽሓፍ ከገጽ  ፪፻፰ ጀምሮ ይመልከቱ)

ወደ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ይኽን ይጫኑት