ቍጥር ፩/፳፻፭ ዓ. ም. የአዋጅ ቃል

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ለዓለሙ ሰዎች፡ ለችግራቸው ኹሉ፡ የመጨረሻው መልስና መደምደሚያው መፍትሔ ኾና ቀርባ ያለችው፡ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ብቻ መኾኗን በተመለከተ።

ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ፡ የሰው ልጆች ምድራዊ ኑሮ፡ የምኞትና የስስት፥ የሲቃና የመቃተት፥ የሥቃይና የመከራ፥ የትንንቅና የዕልቂት እሳትና ማዕበል ያልተለየው፡ የቃጠሎና የድምሳሴ ሰለባ ኾኖ ቆይቷል። ይህም የኾነው፡ በሃይማኖቱና በፍልስፍናው፥ በዘር ማንነትና በቀለም ልዩነት፥ በማኅበራዊው ኑሮና በአገዛዙ ኹኔታ፥ በሥነ ብዕሉ፡ የገንዘብና የሀብት ድልድል፥ እንዲሁም፡ በትምህርት አሰጣጡና በሙያው አሰላለፍ ረገድ ያለው አስተሳሰብና አመራር፡ በማናቸውም መልኩና ይዘቱ፡ ከመሠረቱ፡ ከእግዚአብሔራዊው ሥርዓት፡ ፈጽሞ የተለየ፥ የተዛባና የተቃወሰ ከመኾኑ የተነሣ ነው።

እንዲህ ከኾነ፡ አኹን፡ ይህን የመሰለውን ተስፋ ቢስ አኗኗር፡ ከእነዚህ መሠርይ ጠንቆች አላቅቆና አንጽቶ፡ ነጻ በማድረግ፡ በእነዚህ ቦታ፡ እኩልነትንና ፍትሕን፥ መብትንና ደኅንነትን፥ ሰላምንና ብልጽግናን መተካት፡ እጅግ አስፈላጊ ኾኗል። ለዚህ እውነታ መልካም ፍሬያማነት፡ ሌላ ማማረጫ ከቶ አልተገኘም፤ አይገኝምም፤ የለምና።

ስለዚህ፡ ይህን አዋጅ ያወጀችው፡ ይህችው፡ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ በአፍሪቃ፥ በእስያ፥ በኤውሮጳ፥ በመካከለኛውና በሩቁ ምሥራቅ፥ በሰሜኑ፥ በማእከላዊውና በደቡቡ አሜሪካ፥ በአውስትራልያ፥ በምሥራቃውያኑ እና በምዕራባውያኑ የውቅያኖሶቹ ደሴቶች ክፍላተ ዓለማት ኹሉ፡ ተያይዘውና ተከልለው የሚገኙት አገሮች ተወላጆች፥ ባላገሮችና ኗሪዎች ለኾናችሁት፡ ለእናንተ ወንዶችና ሴቶች፡ ለእያንዳንዳችሁ፡ በነፍስ ወከፍ፡ ይህን የግብዣ ጥሪዋን፡ እነሆ፡ በይፋ እያቀረበችላችሁ ናት።

እናንተም፡ "አንትሙሰ፡ ኅሡ መቅድመ! መንግሥቶ፥ ወጽድቆ፤ ወዝንቱሰ ኵሉ፡ ይትዌሰከክሙ።" ማለትም፡ "እናንተ ግን፡ አስቀድማችሁ፡ የእግዚአብሔርን፡ መንግሥቱን፥ እውነቱን፡ ሹ! ይህም ኹሉ፡ ይጨመርላችኋል።" ያለውን፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን፡ መለኮታዊ ቃል ተከትላችሁ፡ ይህች ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ለቆመችለትና ለምታገለግለው፡ ለዚህ እውነትና እውቀት፥ እምነትና ሕይወት፡ እየራሳችሁን ልታበቁ፡ በቍርጥ የወሰናችሁ ከኾናችሁ፥ ይህንኑ ጥሪዋን ተቀብላችሁ ትፈጽሙታላችሁ። (ማቴ. ፮፥ ፴፫።)

ደግሞም፡ ህልውናችሁ፡ በወንድና በሴት ጾታዎች፡ የተፈጥሮ ኅብረትና
እኩልነት ላይ ተመሥርቶና ጸንቶ፡ ከዚህ የደረሰው፥ ወደፊትም፡ በሚያስተማምን ኹኔታ እንዲህ ሊቀጥል የሚችለው፡ በዚሁ፡ በእግዚአብሔር መንግሥትና እውነት ብቻ መኾኑን፡ የምታምኑ ከኾናችሁ፡ አዎን! በእርግጥ፡ ይህንኑ ጥሪዋን ተቀብላችሁ ትፈጽሙታላችሁ።

ለመሆኑ: ፈጣሪ፡ እንደቃል ኪዳኑ፡ ለዚች፡ ለኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥቱ፡ የወሰናት ቀን ደርሳ፡ በገሃድ እስከሚገልጣችሁና እስከሚያሰባሰባችሁ ድረስ፡ ይህንኑ ጥሪዋን ተቀብላችሁ የምትፈጽሙት እንዴት ነው?

ጥያቄዎችና፡ መልስ ኾነው የተጠቃለሉት ዓበይት ቍም-ነገሮች
፩ኛ. "ኢትዮጵያ" ማናት?
፪ኛ. ኢትዮጵያዊው ማነው? ኢትዮጵያዊቷ ማናት?
፫ኛ. ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?
፬ኛ. "እግዚአብሔር" ማነው?
፭ኛ. "መንግሥት" ምንድን ነው?
፮ኛ. ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ስለመኾኗ።
፯ኛ. ለመኾኑ፡ "የእግዚአብሔር መንግሥት"፡ ምንድን ነው?
፰ኛ. የእግዚአብሔር መንግሥት ሥርዓታዊ አቋም (ሕገ መንግሥት) ምንድን ነው?
፱ኛ. የእግዚአብሔር መንግሥት ኢትዮጵያ፡ መገኛዋ፥ ማደሪያዋና መኖሪያዋ የት ነው?

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከትለው ይቀጥሉ!...