ቍጥር ፲/፳፻፮ ዓ. ም. ቃለ-ዐዋድ።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ሰብኣውያን የዓለም መንግሥታት፡ ዓለማዊ፥ ወይም፡ ሥጋዊ (Secularism) የሚለውን ፍልስፍናቸውን በተመለከተ።

"መለኮታዊ ምዕዳን" - ምዕዳን = ተግሣፅና ማስጠንቀቂያ የተመላበት ትምህርታዊ ምክር ነው።

በሰው ልጆች ህልውና ውስጥ፡ እስከዛሬ ባለፈው፥ አኹን ባለውና ወደፊትም እየተከታተለ በሚደርሰው የዘመን ኺደት፡ ግፍ የተመላበት፡ የክፋትና የኃጢኣት፥ ይህን ዓይነቱም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙ፥ ኹኔታውም ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ መቀጠሉ፡ ለምን እንደኾነ ልታውቁት የሚገባ እውነታ ነው።

መልሱ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥታችን ላይ፡ እስከዛሬ ሲፈጸም የኖረውን፥ ዛሬም፡ እየተካኼደ ያለውን ደባና ጥቃት አጋልጦ በሚያሳየው፡ እንዲህ በሚለው፡ በእግዚአብሔር ቃለ ትንቢት ውስጥ ተጽፎ ስለሚነበብ፡ ይህንኑ ቃል፡ በአንክሮና በተዘክሮ፥ በትኵረትና በተመሥጦ አዳምጡት! አስተውሉትም!

ይህንኛውን መለኮታዊ ምዕዳን፡ ከተቀረው ኹሉ የተለየ ያደረገው መሥፈርት፡ ይኸው መለኮታዊ ምዕዳን፡ በአኹኑ ጊዜ የቀረበው፡ በዐዋጁ አርእስት እንደሚነበበው፡ የየአገሮቹን ሰብኣውያን መንግሥታት በማካተት ሳይኾን፡ በቀጥታ፡ በመላው ዓለም ወደሚኖረው፡ ወደእያንዳንዱ ወንድ፥ ወደእያንዳንዷም ሴት ግለሰብ ብቻ ያተኮረ በመኾኑ ነው። እንግዴህ፡ በመላው ዓለም ለምትገኙ፡ ለእያንዳንዳችሁ ወንድና ሴት ግለሰቦች የምላችሁን ስሙኝ!

በሕይወተ-ነፍስ ዕውቀታችሁ፥ በሕይወተ-ሥጋ ህልውናችሁና በሕይወተ- መንፈስ ብቅዓታችሁ፡ ይኸው፡ እየኖራችሁበትና በእውን እየተመለከታችሁት ያለውን፥ እየራሳችሁን የሚጨምረውን፡ ይህን፡ የሚታየውንና የማይታየውን፥ ረቂቁንና ግዙፉን፥ ሥጋዊዉንና መንፈሳዊዉን፥ ሰማያዊዉንና ምድራዊዉን፥ የሚንቀሳቀሰውንና የማይንቀሳቀሰውን ፍጥረታተ-ዓለማትን ኹሉ የፈጠረ፥ እናንተ እያንዳንዳችሁም፡ በየቋንቋችሁ፡ ስም ሰጥታችሁት የምታመልኩት፥ ነገር ግን፡ ከጥንቶቹ እስከዛሬዎቹ ድረስ፡ ታማኞች ልጆቻችን በኾኑት፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ዘንድ፡ "እግዚአብሔር" ተብሎ የሚጠራው፡ አንድ አምላክ መኖሩን፡ ለእየራሳችሁ፡ በእውነት የሚያረጋግጥላችሁ እምነት ካላችሁ፥ ወይም፡ በዚህ እምነት፡ በልዩ ልዩ ምክንያት፡ እስካኹን ሳታምኑ ቆይታችሁ፡ አኹን ግን፡ ልታምኑበት የምትሹ ካላችሁ፡ ለእናንተ፡ ለኹላችሁም፡ ይህን እላለሁ፦

ከኹሉ አስቀድሞ፡ የምንነቱን ዝርዝር፡ ወደፊት በምታገኙት፡ በመለኮታዊው የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖት አጽድቃችሁ የምታጸኑትን፡ ይህን፡ አኹን የሰማችሁትን እምነታችሁን፡ በውስጣችሁ፡ ፍጹምና እውን አድርጉት! በምግባርም፡ በገሃድ፡ በሥራ፡ የምትገልጡት ይኹን።

ቀጥሎ፡ የየግል ሰውነታችሁን፡ በማወቅ ኾነ፡ ባለማውቅ፥ በፈቃዳችሁም ኾነ፡ ያለፈቃዳችሁ፡ በሰብኣዊው ሕጋችሁ መሠረት፡ በነፍስ፥ በሥጋና በመንፈስ፡ ጽኑ አማኞቹ፥ ሙሉ ዜጎቹና ፍጹም ታዛዦቹ አድርጋችሁና አሳልፋችሁ ከሰጣችሁት፡ ከእየአገሮቻችሁ፡ ሰብኣዊ መንግሥት፡ የእምነት፥ የተገዢነትና የባርነት ቀንበር፡ እየራሳችሁን፡ አኹንም እንደገና፡ በገዛ ፈቃዳችሁና ምርጫችሁ፡ ከላይ በገለጣችሁትና ባረጋገጣችሁት ሃይማኖታችሁ አማካይነት፡ በእግዚአብሔር እውነትና መንፈስ፡ ፈጽማችሁ፡ ነጻ አውጡ።

በመጨረሻ፡ እንዲህ አድርጋችሁ፡ ከእነዚሁ፡ ከእየአገሮቻችሁ፡ ሰብኣውያን የዓለም መንግሥታት፡ የዜግነትና የተገዢነት ቀንበር፡ በነፍስ፥ በሥጋና በመንፈስ፡ ነጻ ያወጣችሁትን፡ የኹለንተና ሰውነታችሁን፡ አኹንም እንደገና፡ በገዛ ፈቃዳችሁና ምርጫችሁ፡ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኳችሁ አማካይነት፡ ለእኛ፡ ለኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ መልሳችሁ ታስረክቡናላችሁ።

ጥያቄዎችና፡ መልስ ኾነው የተጠቃለሉት ዓበይት ቍም-ነገሮች
፩ኛ. "ሕዝባዊ አገዛዝ" [Democracy] እና "ከፋፍለህ ግዛ!" የሚሉት ፍልስፍናዎች፡ ምንድር ናቸው?
፪ኛ. ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ከምታደርገው በጎ ጋር፡ ሰብኣውያን መንግሥታት የሚያደርጉት፡ ሊነጻጸር አይችልም።
፫ኛ. ሥነ ፍጥረት፡ ስትገልጥ የኖረችውን ምሥጢሯን አለማወቅ ይጎዳል።
፬ኛ. የዐዋጅ ቃሌ፤ ስለ"ሦስተኛው" የዓለም ጦርነታችሁ።
፭ኛ. ከዚህ የመጨረሻ ታላቅ መከራና ጥፋት የምታድናችሁ፡ ይህች "ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት"፡ ማን ናት? እርሷን ያልኾነችው ሌላዪቱስ፡ ማን ናት?
፮ኛ. እውነተኞቹ "የእስራኤል ልጆች" "የኢትዮጵያ ልጆች" ስለመኾናቸው።
፯ኛ. የእስልምና ሃይማኖት፡ በምድር ላይ የመከሠቱ ምሥጢራዊ ዓላማ።

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...