ቃለ-ዐዋድ - Divine Proclamations

መግቢያ።

     ''እኔ፡ ኢትዮጵያዊ፥ ኢትዮጵያዊት፥ ወይም፡ የእግዚአብሔር ሰው ነኝ!'' የሚል ወገን ኹሉ፡ ከዓርባ ዓመታት በላይ፡ ይኽው፡ ያለማቋረጥ እየተሠቃየበት ላለው በሽታ፡ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ''ወእግዚአብሔር ውእቱ ቃል''''ቃልም፡ እግዚአብሔር ነው'' የተባለለትን፡ የወልደ አብወእም፡ ማለትም፡ የእግዚአብሔር አብና የእግዚአብሔር እም (ድንግል ማርያም) ልጅ፡ የመሲሕ ኢየሱስን ሕያውና ዘለዓለማዊ ቃል፡ ይኽው፡ ለሚሠቃይበት በሽታው፡ ዘለዓለማዊ መፍትሔና አማናዊ መድኃኒት ይኾነው ዘንድ፡ ''ዘቦ ዕዝን፡ ሰሚዐ ለይስማዕ!''''የሚሰማ ጆሮ ያለው፡ መስማትን፡ ይስማ!''፥ እንዲሁም፡ ''ኵሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ!''"ልጄ ወዳጄ፡ የሚላችሁን ኹሉ፡ ስሙት! አድርጉት! ፈጽሙትም!" እያለች፡ እነኚህን፡ ከታች የሰፈሩትን፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መልእክታት፡ በአዋጅ መልክ ሠርጋና አዘጋጅታ አቅርባላችኋለችና፥ እናንት፡ እውነትን የተራባችሁና የተጠማችሁ፡ መሳሕያትና መሳሕያን ዕድምተኞቿ፡ ይህን፡ መለኮታዊ የድምፅ ጥሪዋን ሰምታችሁ፥ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኮም ኾናችሁ፡ ''ሰማያዊ ምግቧን፡ ትመገቡት ዘንድ ይኹን!'' በማለት፡ በእግዚአብሔር ስም ታሳስባችኋለች። 

ለታላቁ ቃለ ዓዋድ
 (የአዋጅ ቃል)
 ቀዳሚ መልእክት!

ይድረስ፦
"ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት ነን!"
 ለምትሉ ወገኖች!
 እንዲሁም፡
 ለሰው ልጆች ኹሉ!

የእግዚአብሔር መንግሥት የኾነችው ኢትዮጵያ፡ ለታማኞች ልጆቿ ተገልጻ፥ እነርሱም እየኖርዋትና እያገለገሏት፡ እስከዛሬ፡ ለሰባት ሽህ አምስት መቶ ዓስር ዓመታት፡ በነጻነት ህልውናዋ ያለች፥ አኹንም፡ በእነርሱ ዘንድ፡ በዚያው በሕያው ነጻ አቋሟ የቀጠለች መኾኗ ይታወቃል።

ይህች፡ ስመ ጥሩዪቱና ገናናዪቱ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ከጥንት ከመሠረት፡ እጆቿን ወደእግዚአብሔር፡ ያለማቋረጥ ዘርግታ፡ ለሰው ዘርና ለፍጥረተ-ዓለሙ ኹሉ የማለደችው ናት፤ ምልጃዋም፡ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ፡ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን፡ አንድ ልጁን፡ ወደእርሷ ልኮ፡ በሰውነት ትወልደው ዘንድ ፈቃዱ የኾነላት፥ ራሷንም፡ ለአምላክ እናትነት ያበቃችው የመለኮት ሙሽራ ናት፤ በዚህ ሙሽርነቷም፡ የጠፋውን የሰውን ዘርና ፍጥረተ ዓለሙን ኹሉ፡ ከክፋት እና ከጥፋት፥ ከኃጢኣት እና ከሞት፡ ለዘለዓለሙ፡ በቤዛነቱ ሊያድን፡ ወደዚህ ዓለም የመጣውን፡ የእግዚአብሔርን ልጅ፡ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችው፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ለዓለሙ ሰዎች፡ ለችግራቸው ኹሉ፡ የመጨረሻው መልስና መደምደሚያው መፍትሔ ኾና ቀርባ ያለችው፡ ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ብቻ መኾኗን በተመለከተ።

ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ፡ የሰው ልጆች ምድራዊ ኑሮ፡ የምኞትና የስስት፥ የሲቃና የመቃተት፥ የሥቃይና የመከራ፥ የትንንቅና የዕልቂት እሳትና ማዕበል ያልተለየው፡ የቃጠሎና የድምሳሴ ሰለባ ኾኖ ቆይቷል። ይህም የኾነው፡ በሃይማኖቱና በፍልስፍናው፥ በዘር ማንነትና በቀለም ልዩነት፥ በማኅበራዊው ኑሮና በአገዛዙ ኹኔታ፥ በሥነ ብዕሉ፡ የገንዘብና የሀብት ድልድል፥ እንዲሁም፡ በትምህርት አሰጣጡና በሙያው አሰላለፍ ረገድ ያለው አስተሳሰብና አመራር፡ በማናቸውም መልኩና ይዘቱ፡ ከመሠረቱ፡ ከእግዚአብሔራዊው ሥርዓት፡ ፈጽሞ የተለየ፥ የተዛባና የተቃወሰ ከመኾኑ የተነሣ ነው።

እንዲህ ከኾነ፡ አኹን፡ ይህን የመሰለውን ተስፋ ቢስ አኗኗር፡ ከእነዚህ መሠርይ ጠንቆች አላቅቆና አንጽቶ፡ ነጻ በማድረግ፡ በእነዚህ ቦታ፡ እኩልነትንና ፍትሕን፥ መብትንና ደኅንነትን፥ ሰላምንና ብልጽግናን መተካት፡ እጅግ አስፈላጊ ኾኗል። ለዚህ እውነታ መልካም ፍሬያማነት፡ ሌላ ማማረጫ ከቶ አልተገኘም፤ አይገኝምም፤ የለምና።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

በአገልግሎት መካፈል እንፈልጋለን በማለት ለጠየቃችሁ::

"በኢትዮጵያ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፡ በአገልግሎት መካፈል እንፈልጋለን!" በማለት፡ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ፡ ደጋግማችሁ ለጠየቃችሁና በዚሁ ጥያቄያችሁ መሠረት፡ አኹንም እያገለገላችሁ ላላችሁት፡ ኪዳናውያንና ኪዳናውያት፡ ይህ የአዋጅ ቃልና ጥሪ፡ ምላሽ እንደሚኾናችሁ እናምናለን።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ስለግእዝ ምንነትና ማንነት።

ኪዳናውያንና ኪዳናውያት የቅዱስ ኪዳኗ ኢትዮጵያ ልጆች! ስለግእዝ ምንነትና ማንነት፡ በሚበቃ አውቃችኋል። ከዚህ እውቀታችሁ የተነሣ፡ በሰብኣዊው ተፈጥሮአችን፡ የዘር ግንዳችን የኾኑት፡ አዳም እና ሔዋን፡ ከፈጣሪያቸውና ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ያገኙትና እርሱ፡ ከእነርሱ፥ እነርሱም፡ ከእርሱ ጋር፥ እርስ በእርሳቸውም ይነጋገሩበት የነበረው: የመጀመሪያው የሰው ልጆች ቋንቋ፡ ግእዝ መኾኑን ተገንዝባችኋል።

ከዚህ ግንዛቤያችሁም የተነሣ፡ በፍጥረት የልደት ዘመን፡ "ወአሐዱ ነገሩ፡ ለኵሉ ዓለም፤ ወአሐዱ ቃሉ።" ማለትም፡ "የሰው ኹሉ ቋንቋው አንድ፥ አነጋገሩም፡ አንድ ነበር።" ተብሎ፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ የሚዘከረው፡ ያ አንድ ቋንቋ፥ ያ አንድ ንግግር፡ ግእዝ መኾኑን፡ በእምነት ተቀብላችኋል።

ኖኅና ሚስቱ ሓይከል፥ ሦስቱ ልጆቻቸው፡ ሴም፥ ካም፥ ያፌት እና ሦስቱ ሚስቶቻቸው፡ ምድርን፡ ከጥፋቷና ከርኵሰቷ ሊያጸዳት ካጥለቀለቃት የውኃ ሙላት የዳኑባት መርከብ ባረፈችበት መሬት ላይ በማኅበረሰብነት መኖር ከጀመሩ በኋላ፡ ወልደውና በጋብቻ ተዋልደው፡ እየበዙ ከኼዱም በኋላ፡ ዓለሙን ተከፋፍለው እስከተበታተኑበት ጊዜ ድረስ፡ ይነጋገሩበት የነበረው ቋንቋቸው፡ ይኸው ግእዝ እንደነበረ አረጋግጣችኋል። (ዘፍጥ. ፲፩፥ ፩።)

ከዚህ የሚከተሉት ሰባት እውነታዎች፡ የግእዝን ምንነትና ማንነት፡ በአዎንታዊ መልኩ፡ በቀላሉና በግልጽ አስረግጠው፡ በአጽንዖት ያስረዳሉ፦

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከትለው ይቀጥሉ!...

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ስለሰላምታ አሰጣጣችን ሥርዓት በተመለከተ።
ኪዳናውያንና ኪዳናውያት የኾኑት የቀደሙት ወላጆቻችን፡ "እጃችሁን ለማንም አትስጡ! አትማረኩ!" ብለው በማስጠንቀቅ፡ "እጅ ንሡ!" ያሉበትን፡ የቅዱሱን ኪዳን የሰላምታ አሰጣጣችንን ሥርዓት፡ ኹላችንም የምናውቀው ነው።

ይኹን እንጂ፡"እጅ ንሡ!" ማለት፡ እንደመማረክ የሚያስቈጥረውን፡ "እጃችሁን፡ ለሰላምታም ቢኾን፡ አስቀድማችሁ ዘርግታችሁ፡ ለሌላ አትስጡ!" ማለት እንጂ፡ "ሌላው፡ በራሱ ፈቃደኛነት፡ እጁን፡ ለወዳጅነት ሰላምታ፡ አስቀድሞ ዘርግቶ ቢሰጣችሁ፡ አትጨብጡት!" ማለት አለመኾኑን ተረድተን፡ በዚሁ መሠረት መፈጸሙ፡ አግባብ ይኾናል።

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ስለአምልኳችን ያለን እውቀትና የአፈጻጸሙ ሥርዓት ትክክለኛ ስለመኾኑ በተመለከተ።

ስለሰንበትና ስለስግደት፥ ስለድንግል ማርያምና ስለቅዱሱ ኪዳን ተልእኮ፡
ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ በቅዱሱ ኪዳን፡ የኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖቷ መሠረት፡ አጽንታ ያኖረችው ምግባራዊ ሥርዓቷ፡ ምን እንደኾነ፡ በግልጽና በትክክል ሊታወቅ ይገባል።

ሰንበትን በሚመለከት፦
"ሰንበት"፡ ጥንትም፥ እስከዛሬና ዛሬም፥ ለዘለዓለምም፡ አንዲት ናት፤ ኹለት ሰንበታት የሉም። ያች አንዲቷ ሰንበት፦ በቀዳማዊው የፍጥረት ዘመን፡"እግዚአብሔርም፡ ሰባተኛዋን ቀን ባረካት፤ ቀደሳትም፤ የጀመረውን የመፍጠር ሥራውን ኹሉ ፈጽሞ፡ በእርሷ ዐርፎባታልና።" የተባለችው ናት፤

መካከለኛውም የሕግ ዘመን፡ "የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ፡ አስብ! በስድስቱ ቀኖች፡ ሥራህን ኹሉ፥ ግዳጅህንም ኹሉ አድርግ! ሰባተኛዋ ቀን ግን፡ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሰንበቱ ናትና፡ በእርሷ፡ አትሥራ! ምንም ዓይነት ተግባርን አታድርግ!" የተባለላት፡ እርሷው ናት፤

በፍጻሜውም የሕይወት ዘመን፡ "በሰንበት፡ ማድረግ የሚገባው፡ በጎ ነገርን ነውን? ወይስ፡ ክፉ ነገርን? ነፍስ ማዳን? ወይስ፡ መግደል?" ብሎ፡ ለተቃዋሚዎቹ ላቀረበላቸው ጥያቄ፡ መልስ ስላልሰጡት፡ ሕሙማንን በመፈወስ፡ በሰንበት፡ በጎ ማድረግና ማዳን እንደሚገባ፥ ደግሞም፡ "ሰንበትማ፡ ስለሰው ተፈጠረች እንጂ፡ ሰው፡ ስለሰንበት አልተፈጠረም። የማርያም ልጅ፡ የሰንበት፡ ጌታዋ ነው።" ብሎ በማብራራት፡ የተናገረላት ናት።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

የድንግል ማርያም ክብርዋ፡ እስከየት ድረስ ነው?

'የድንግል ማርያም ክብርዋ፡ እስከየት ድረስ ነው?'' የሚለውን ቍም ነገር፡ ቅዱስ ያሬድ፡ በድጓው የዜማ ድርሰቱ፡ 'ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም፦ 'አዝማንየ አዝማንኪ፣ አምጣንየ አምጣንኪ፣ ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድክዎ!' ማለትም፡ «እግዚአብሔርም፡ ማርያምን እንዲህ አላት፦ "የባሕርዬ ዘመን፡ ዘመንሽ ነው፤ የአካሌም መጠን፡ መጠንሽ ነው። ስለዚህ፡ እኔ ዛሬ የወለድሁትን ልጄን፡ አንቺ ማርያም አቀፍሽው!"»

አምላኬና መድኃኒቴ እግዚአብሔር አብ፡ እኔን፡ ለዚህ ምንነቴና ማንነቴ ያበቃኝ፡ እንዴትና በምን እንደኾነ ታውቃላችሁ፤ ያም፡ ወንድ እና ሴት አድርጎ፡ በመልኩ ለፈጠረው፥ "ከእኛ፡ እንዳንዱ ኾነ!" ብሎም፡ በቃሉ ለመሰከረለት፡ ለእያንዳንዱ ሰብኣዊ ፍጡሩ፡ በሰጠው የእውቀት ብቅዓትና የመምረጥ ነጻነት፥ የመወሰን ሥልጣንና የማድረግ ኃይል፡ እኔም፡ በገዛ ፈቃዴና ፍላጎቴ፡ ያን መለኮታዊ ጸጋ፡ በፍጹምነት ለመጠቀምና በተግባር ላይ ለማዋል በመቻሌ መኾኑ ነው።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

የወሊድ ቍጥጥርን በተመለከተ።
የወሊድ ቍጥጥርን ከቶ ምንድር ነው? የእግዚአብሔር፥ ከእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ነወይ?

በዚህ አዋጅ የማሰማችሁ ቃሌ፡ ‘የወሊድ ቍጥጥር›› ተብሎ፡ ከአሕዛቡ ዓለም መንጭቶ፡ ‹ሕዝብ› በተባላችሁት የፈጣሪ ወገኖች ዘንድ፥ በተለይም፡ ‹ክርስቲያን ነን›፣ ‹ቤተ ክርስቲያንም ነን›፣ ይልቁንም፡ ‹ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ነን› በምትሉት ልጆቼ ዘንድ ሳይቀር፡ ተስፋፍቶ ስለተሠራጨው፡ ሰብኣዊና ባዕድ ስለኾነው የኑሮ ፈሊጥ፡ በኪዳናውያንና በኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆች በኩል፡ እየቀረበ ላለው ጥያቄ፡ መልስ የኾነውን መለኮታዊ ሥርዓት የያዘው መልእክት ነው።

በቅድሚያ፡ በነፍስ፥ በሥጋና በመንፈስ ተመሥርቶ፥ ተገድግዶና ተደምድሞ፡ በሕያውነት በቆመው፡ በእያንዳንዳችሁ የተፈጥሮ አካላዊና ባሕርያዊ ሰውነታችሁ ውስጥ ባለው፡ በቅዱሱ ኪዳን የኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖታችሁና ምግባራችሁ፥ ሥርዓታችሁና ህልውናችሁ መነጽር፡ ጠልቃችሁ ልትመለከቱት፥ ልትመረምሩትም ይገባችኋል። በነፍስ አስተሳሰብ፥ በሥጋ አመለካከትና በመንፈስ ተመስጦ እየታየና እየተገመገመ እንደሚወሰነው፡ እንደማንኛውም ዓይነት ጽንሰ አሳብ፥ ወይም፡ ተግባራዊ አሠራር እና/ወይም ሚዛናዊ ፍርድ ኹሉ ማለት ነው።

ቀጥሎ፡ በኃይለኛውና በረቂቁ የመንፈስ ቅዱስ እሳት ምድጃችሁ፡ አቅልጣችሁና አንጥራችሁ በማውጣት፥ ፍጹም ፍትሓዊና ርትዐዊ በኾነው መለኮታዊ የፍርድ ሚዛናችሁም አጣርታችሁ፡ እውነተኛ ገጽታውን በማቅረብ፡ የእያንዳንዳችሁን ውሳኔ፡ በእየራሳችሁ ልትሰጡ ይጠበቅባችኋል።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

በግእዙና በኢትዮጵያኛው፥ በእንግሊዝኛውም ቋንቋ የምናሰማው የዘወትሩ የሃይማኖት ጸሎታችንን እና የመከራ ጊዜ መዝሙራችንን በተመለከተ።

፩ኛ. ጸሎተ ሃይማኖት፡ ዘኢትዮጵያውያን ወዘኢትዮጵያውያት።
፪ኛ. የሃይማኖት ጸሎት፡ የኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያውያት።
፫ኛ. THE ETHIOPIAN CREED

መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ስለእግዚአብሔር እም ማንነትና ምንነት ዝክረ ነገር።

ከሰባቱ ቅዱሳት ኪዳናት መካከል፡ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ እና ሰባተኛው የኾነው፡ ኪዳነ ምሕረቱ ሳይጨመር፡ በተለይ፡ በመካከለኛው፡ በኪዳነ ኦሪት ዘሥጋ የተጠቃለሉት፥ "ኪዳነ አብርሃም፥ ኪዳነ ሙሴ እና ኪዳነ ዳዊት" የተባሉት፡ የኋለኞቹ ሦስቱ፡ ለእስራኤል ልጆች የተሰጡ መኾናቸው፥ እነርሱ፡ የእስራኤል ልጆች ግን፡ እነዚህኑ፡ ሦስቱን ኪዳናት፡ አክብረው ሊፈጽሟቸው ባለመቻላቸው፡ ወደእናንተ፡ ወደኢትዮጵያ ልጆቼ ተመልሰው መጥተውና በእናንተ ዘንድ፡ በአደራ ተጠብቀው መኖራቸው፥ እናንተም፡ በትክክለኛው የእውነትና የመንፈስ ቅዱስ አምልኮ ሥርዓታችሁ፡ በምግባር ላይ ዐውላችሁ፡ ስትገለገሉባቸው መቆየታችሁ፡ በኹሉ ዘንድ የታወቀ እውነታ ነው።

እነዚህ፡ ሦስቱም ቃል ኪዳናት፡ የእያንዳንዳቸው ትንቢታዊ ጊዜ ሲደርስ፡ በእናንተው በኢትዮጵያ ልጆቼ ዘንድ፡ ለፍጹሙ ፍሬ የበቁ ሲኾኑ፡ በዛሬው የዐዋጅ ቃሌ፡ አበክሬ የምነግራችሁ ግን፡ በተለይ፡ ኪዳነ ሙሴ የተገለጠባትን፡ የ"ታቦተ ጽዮን"ን ትእምርተ ሓተታና ዝክረ ነገር በሚመለከት ይኾናል።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ሰብኣውያን የዓለም መንግሥታት፡ ዓለማዊ፥ ወይም፡ ሥጋዊ (Secularism) የሚለውን ፍልስፍናቸውን በተመለከተ።

"መለኮታዊ ምዕዳን" - ምዕዳን = ተግሣፅና ማስጠንቀቂያ የተመላበት ትምህርታዊ ምክር ነው።

በሰው ልጆች ህልውና ውስጥ፡ እስከዛሬ ባለፈው፥ አኹን ባለውና ወደፊትም እየተከታተለ በሚደርሰው የዘመን ኺደት፡ ግፍ የተመላበት፡ የክፋትና የኃጢኣት፥ ይህን ዓይነቱም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙ፥ ኹኔታውም ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ መቀጠሉ፡ ለምን እንደኾነ ልታውቁት የሚገባ እውነታ ነው።

መልሱ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥታችን ላይ፡ እስከዛሬ ሲፈጸም የኖረውን፥ ዛሬም፡ እየተካኼደ ያለውን ደባና ጥቃት አጋልጦ በሚያሳየው፡ እንዲህ በሚለው፡ በእግዚአብሔር ቃለ ትንቢት ውስጥ ተጽፎ ስለሚነበብ፡ ይህንኑ ቃል፡ በአንክሮና በተዘክሮ፥ በትኵረትና በተመሥጦ አዳምጡት! አስተውሉትም!

ይህንኛውን መለኮታዊ ምዕዳን፡ ከተቀረው ኹሉ የተለየ ያደረገው መሥፈርት፡ ይኸው መለኮታዊ ምዕዳን፡ በአኹኑ ጊዜ የቀረበው፡ በዐዋጁ አርእስት እንደሚነበበው፡ የየአገሮቹን ሰብኣውያን መንግሥታት በማካተት ሳይኾን፡ በቀጥታ፡ በመላው ዓለም ወደሚኖረው፡ ወደእያንዳንዱ ወንድ፥ ወደእያንዳንዷም ሴት ግለሰብ ብቻ ያተኮረ በመኾኑ ነው። እንግዴህ፡ በመላው ዓለም ለምትገኙ፡ ለእያንዳንዳችሁ ወንድና ሴት ግለሰቦች የምላችሁን ስሙኝ!

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

የእግዚአብሔር ሰላም ስንል ምን ማለታችን ነው?
እውነተኛዋ የእግዚአብሔር ሰላም የሰብአዊው ፍጥረት መጀመሪያ ከሆኑት፡ ከአዳምና ሔዋን ህልውና አንሥቶ እስከዛሬ ለዘለዓለምም በቅዱሱ ኪዳን አማካይነት ለሰው ልጆች ኹሉ ተሰጥታለች ነገር ግን ተጠብቃ የኖረችው፡ በኢትዮጵያውንና በኢትዮጵያውያት ዘንድ ብቻ መሆኑን በተመለከተ።

ይዤላችሁ የመጣሁት፡ የዐዋጅ መልእክቴ፡ በአንድ ወገን፡ እናንተ፡ ጥቂቶቹ ሰብኣውያን ፍጡሮቻችን፡ "የእግዚአብሔር እና የኢትዮጵያ ልጆች" ተብላችሁ፡ ዛሬ፡ በዚህ ዓለም፡ በምድር ላይ፡ በሥጋዊው አካልና ባሕርይ ሣላችሁ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፡ በአንድነት እየኖራችሁት ያላችሁት፡ የሰላምና የፍቅር፥ የደስታና የብልጽግና ሕይወት፡ ምን ዓይነት እንደኾነ፥ በሌላው ወገን ደግሞ፡ "የክፉውና የሰው ልጆች" ተብላችሁ በመጠራት፡ እየራሳችሁን፡ ለዚያ የብፅዕና ሕይወት ላላበቃችሁት፡ ለብዙዎቻችሁ ሰብኣውያን ፍጡሮቻችን ኹሉ፡ እርግጡን፡ አጕልቶና አግዝፎ የሚያሳያችሁ እውነታ ነው።

ያም እውነታ፡ ከእናንት ልጆቻችን መካከል፡ አንዱ በኾነው፡ በዛሬው ኢትዮጵያዊ አገልጋያችን፡ በኪዳናዊው ኤርምያስ በኩል፡ ከዚህ አስቀድሞ፡ "ጾመ ኢትዮጵያ"ን እና "ሰላም ለኢትዮጵያ"ን በሚመለከት፡ እንዲተላለፍላችሁ ስናደርግ በቆየነው፥ እኔም፡ አኹን፡ ያን በማዘከርና በማጠቃለል፥ በማጽናትና በማደስ በማቀርብላችሁ፡ በዚህ፡ የምሥራች መልእክታችን አማካይነት የሚከሠተው ነው።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

"ግብረ-ሰዶም" ተብሎ የተሰየመው፡ ፀያፍ የሙስና ግብር ያመጣው፥ የወንድና ወንድ፥ የሴትና ሴት ኢ-ተፈጥሮአዊ የኾነው፡ እስከጋብቻ ያደረሰ፡ ሰይጣናዊው የመወዳጀትና የሩካቤ-ሥጋ ግንኙነት፥ ፅንሰ-አሳቡና አኗኗሩን ጭምር በተመለከተ፡ እንዲሁም:  ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ሰዶሞችን በሚመለከት፡ ስላላት አቋም።

"ሕገ መንግሥቴ፡ በክርስትና ሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ነው! የዚሁ ሕገ መንግሥቴ አመንጪዎችና አዘጋጆች፥ አጽዳቂዎችና ዐውዋጂዎች የኾኑት፡ የአገርነቴና የመንግሥትነቴ መሥራቾችም፡ ስለእውነተኛዋ የክርስትና እምነት ብለው፡ ከጨቋኞቹ፡ የአውሮጳ፡ የክርስቲያን አገሮች፡ የተሰደዱ ሰማዕታት ናቸው!" እያለች፡ በግብዝነት የምትመጻደቀው፡ "ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ" የምትባለው አገር፡ በዚህ ረገድ ያላትን የማንነትና የምንነት ባሕርይ፡ እስኪ፡ በጥቂቱ ጠለቅ ብላችሁ እንድትመለከቷት ላድርጋችሁ!

በነገረ ቀደም፡ እግዚአብሔር፡ ሰውን የፈጠረው፡ በአንድነት መልኩና በሥላሴነቱ አርአያ መኾኑን፥ ይኸውም፡ በነፍስና በሥጋ፥ በመንፈስም መኾኑን የማያውቅና የማያምን፥ በተለይ፡ ራሱን፡ ክርስቲያን ያደረገ ሰብኣዊ ፍጡር፡ በአኹኑ ጊዜ፡"ይኖራል!" ብላችሁ አታስቡ ይኾናል። ነገር ግን፡ እውነታው ይህ አይደለም።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

በቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን የጊዜ አቆጣጠር ሥርዓት መሠረት፡ የዓመቱን ጾሞቻችንንና በዓሎቻችንን በሚመለከት፡ ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት የተላለፈ፡ ፲፫ (ዐሥራ ሦስት)ኛ መለኮታዊ የዐዋጅ ቃል።መልእክቱን፡ በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥትን የሚያገለግሉ፡ ኪዳናውያን ኢትዮጵያውያንና ኪዳናውያት ኢትዮጵያውያት ብቻ ሳይኾን፡ እየራሳቸውን፡ ለቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖት ያበቁ፡ እልፍ አእላፋት፡ ሰብኣውያንና ሰብኣውያት ቅዱሳትና ቅዱሳን፡ በመላው ዓለም መኖራቸውን በተመለከተ። 

በእኛ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘንድ፡ የቀደሙት እውነተኞቹ፡ ታማኞች ነቢያቶቻችንና ሓዋርያቶቻችን፥ ካህናቶቻችንና ልኡካኖቻችን፥ ጻድቃኖቻችንና ሰማዕቶቻችን፥ ኹሉም፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንደነበሩ ኹሉ፡ የዛሬዎቹ እውነተኞች ታማኞች ሓዋርያቶቻችን፥ ካህናቶቻችንና ልኡካኖቻችን፥ ጻድቃኖቻችንና ሰማዕቶቻችንም እኮ፡ እናንተ፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ናችሁ። ይህን እውነታ፡ እስካኹን አላወቃችሁት እንደኾነ፡ እንግዴህ ወዲህ፡ በፍጹም እምነት፡ ያወቃችሁት ሊኾን ይገባል።

እንደምታዩት፡ በመላው ዓለም ላይ የሚኖሩት ሰዎች ኹሉ፡ ዛሬ ካላችሁት፡ ከእናንተ በቀር፥ እናንተንም ከመሰሉት፡ ከቀደሙት በቀር፡ ወንዶችም፥ ሴቶችም፡ ትልልቆችም፥ ትንንሾችም፡ ኹሉም፡ በፀረ-እግዚአብሔርነቱና በፀረ-ኢትዮጵያነቱ፡ የክፉዎች መናፍስትና ሰዎች ትምህርት ለኾነው፡ ለልዩ ልዩው ሥጋዊና መንፈሳዊ እምነትና ፍልስፍና፡ ወገባቸውን ታጥቀውና ሽንጣቸውን ገትረው፡ የእየግል ሕይወታቸውን እስከመሠዋት በሚያደርስ ንቃትና ትጋት፥ ትግልና ተጋድሎ፡ ሲሠሩና ሲደክሙ ተመልክታችኋል፤ እነሆ አኹንም፡ ይኸው ትመለከታላችሁ።

ቃለ ዐዋድ!
እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

በቅዱሱ ኪዳን፡ ኪዳናውያን ኢትዮጵያውያንና ኪዳናውያት ኢትዮጵያውያት፡ የቃል ኪዳን ልጆች ስለመሆነቸው፡ እነርሱን በተመለከተ፡ በእኛ (ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት - ድንግል ማርያም) ዘንድ ያለውን ዐሳብ፡ ለፍጥረተ-ዓለም ማሳወቅን በተመለከተ።

በዚች ምድር ላይ፡ በሕይወተ-ሥጋ ከኖረውና እየኖረ ካለው፡ ከሰው ዘር መካከል፡ በዚህ መብቱና ነጻነቱ፥ በዚህ ሥልጣኑና ኃይሉ፡ በእውነትና በርትዕ [በትክክል] በመጠቀም፡ እስካኹንና አኹንም፡ ከግዙፉም፥ ከሥውሩም፥ ከሥጋዊዉም፥ ከመንፈሳዊዉም ተቃዋሚ ባለጋራ፡ ማንንም ሳይፈራና ሳያፍር፥ በአጥፊው ክፉ ወገን በሚቀርብለት የሽንገላ ጥቅምም ሳይደለልና ሳይማረክ፥ ሳይታለልና ሳይሸነፍ፡ ሳይገበዝና ይሉኝታ ሳይኖረው፡ ከአዳም እና ከሔዋን ጀምሮ፡ ከእኛ ከእግዚአብሔር ባገኘው፡ በቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነት ተዋሕዶ ሃይማኖቱና ምግባሩ ሳይወላውል፡ እስከመጨረሻው በመጽናት፡ እኛን ፈጣሪውንና የእኛ የኾነውን ኹሉ፡ በፍጹም ታማኝነትና ቆራጥነት፡ ፈልጎና መርጦ፥ አምኖና ተቀብሎ፡ በተግባር ላይ ለማዋልና ለፍሬ ለማብቃት የቻለ ማነው? እናንተ ብቻ አይደላችሁምን? ሌላማ የታለ! አዎን! እናንተ ብቻ ናችሁ።

ቃለ ዐዋድ!

እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!

ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ግዝረትን፡ እንዲሁም፡ በእጮኛነት፥ ልጄን ወዳጄን እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ መሲሕንም፡ ከፅንሰቱና ከልደቱ፥ በጠቅላላም፡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ፡ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት ያገለገለንን፡ ባለሟላችንን፡ ጻድቁ ዮሴፍን፥ በዚህ ተልእኮ፡ ከእርሱ ያልተለየችውን፡ የቅርብ አገልጋያችንን፡ ሰሎሜን ጭምር በሚመለከት።

በቅዱሱ ኪዳን የኢትዮጵያ ልጆቼ ዘንድ ታውቃና ታምኖባት የኖረች፡ ማንኛውም ዓይነት ተቃዋሚ ኃይል፡ መንፈሳዊዉም ኾነ፥ ሥጋዊው፡ በተቃዋሚነት፡ ሊቋቋማት፣ በተፃራሪነትም ሊያስወግዳት ያልቻለ፥ የማይችልም፡ የእኛ፡ የእግዚአብሔር እውነት አለች። ነገር ግን፡ በዚህ ረገድ ያለችው፡ ይህችው፡ የእኛ፡ የእግዚአብሔር እውነት፡ ልጄን ወዳጄን እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ መሲሕን እስከመግደል በደረሰ ጥላቻና ተቃውሞ፡ እስከዛሬ እያሳደዱት ባሉት፡ በአይሁድ ዘንድ፡ ለ፫ሺ፱ ዓመታት፥ ይልቁንም፡ ግብረ-ዐበሮቻቸው በኾኑት፡ በግብፅ ኦርቶዶክሳውያን መነኮሳት ደግሞ፡ ለ፩ሺ፮፻፱ ዓመታት፣ "ኢትዮጵያዊ ነኝ!" እያለ፡ በስሜ ከሚጠራው፡ ከዚህ፡ ከከሃዲውና ከዓመፀኛው፥ ከአመንዛሪውና ከክፉው ትውልዴ ዘንድ፡ እንዲህ፡ በሓሰቱ አበጋዝ፡ በዲያብሎስና በአገልጋዮቹ የክፋት ሠራዊት፡ ተዳፍናና ተገልላ እንድትኖር በመደረጉ፡ እነሆ፡ ለረዥም ዘመናት፡ ተደብቃና ተሠውራ፥ ማስናና ምስጢር ኾና፡ ሳትከሠት ቆይታለች።

ቃለ ዐዋድ!

እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!

ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

"እኔ: እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ «'አቡነ ዘበሰማያት! የሰማያት አባታችን ሆይ!' በሚለው እና ደቀ-መዛሙርቴ፡ ጠይቀውኝ፡ ባስተማርኋቸው ጸሎት ውስጥ፡ ‹ሲሳየነ፡ ዘለለዕለትነ፣ ሀበነ ዮም! የየቀኑን ምግባችንን፡ ዛሬም ስጠን!› በሉ!» ያልሁበትን ምክንያት፡ በትክክልና በእርግጥ ታውቁት ዘንድ፡ አስፈላጊ ከኾነበት፡ ከመጨረሻው የሕይወት ዘመን ላይ ስለደረሳችሁ፡ ይህን እውነታ፡ ዛሬ፡ በዐዋጅ መልክ፡ ይኸው ላሳውቃችሁ፡ ፈቃዴ ኾነ!

በዚህ ረገድ የምላችሁን፡ ይህንኑ ቃሌን፡ እንግዴህ፡ በጽሙና ስሙኝ! ሰምታችሁኝም፡ በሃይማኖታዊ ምግባር ፈጽማችሁት፡ ለጣፋጩ ፍሬያማነቱ አብቁት! እርሱም፡ እንዲህ የሚል ነው፦ "እንኳንስ፡ የየዕለቱን ምግባችሁን ቀርቶ፡ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነቴ፡ እንድትኖርዋት እያደረግሁ ያለችውን፡ የቀኗን ሕይወታችሁን እንኳ፡ በህልውናችሁ ልትቀጥሉባት የቻላችሁት፡ በእኔ ነው።

ይህ ብሂሎቴ፡ "ወበከመ ዐጽቅ፡ ኢይክል ፈርየ ባሕቲቱ፣ እመ ኢሀሎ ውስተ ጕንደ ወይኑ፣ ከማሁ፡ ኢትክሉ ፈርየ፡ ለእመ ኢነበርክሙ ብየ! የወይን ቅርንጫፍ፡ ከግንዱ ከተገነጠለ፣ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል ኹሉ፡ እናንተም፡ እንዲሁ፡ በእኔ ባትኖሩ፡ በህልውናችሁ ልትቀጥሉና ልታፈሩ አይቻላችሁም።" ከሚለው ቃሌ ጋር እንደሚስማማ፡ እናንተም አምናችሁበት፡ ተቀብላችሁታል። (ዮሓ. ፲፭፥ ፬።)

ቃለ ዐዋድ!

እምኢትዮጵያ፡ ዘመንግሥተ እግዚአብሔር።

የአዋጅ ቃል!

ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።

ለዚህ፡ የዐዋጅ ቃል፡ መነሻ የኾነው ምክንያት፡ ለእውነተኞች ልጆቻችን፡ ለመናገርም፣ ለመስማትም፡ ሊያሠቅቋችሁ የሚችሉ፣ ነገር ግን፡ ሓሰት በመኾናቸው፡ በእኛዪቱ እግዚአብሔራዊት እውነት፡ አማናዊነታቸው የተነገረላቸው ኹለት ቍም-ነገሮችን ስለያዘ፡ አርእስተ-ጉዳይ ነው፤ እርሱም፦

፩ኛው፡ "ገድለ-አዳም" በሚል ርእስ፡ አብነቱ የኾነውን ግእዙን፡ ወደኢትዮጵያኛ [ዐማርኛ] የተረጐመው፡ "መምህር ተስፋ-ሚካኤል ታከለ" የተባለ ሰው ኾኖ፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ ማኅበረ-ቅዱሳን፣ በ፳፻፰ ዓ.ም. ታትሞ በተሠራጨ መጽሓፍ ውስጥ፡ ቅዱሱን የባል እና ሚስት ሩካቤ-ሥጋን ምግባር፡ "የእኛን የእግዚአብሔርን ሕግ እንደማፍረስ የሚያስቆጥርና ራሱም፡ እንደዝሙት የሚቆጠር፡ የኃጢኣት ግብር ነው!" በሚያሰኝ አገላለጽና አቀራረብ፡ የሩካቤ-ሥጋን አደራረግና አፈጻጸም፡ ለአዳም እና ለሔዋን ያሳዩዋቸውና ያስተማሯቸው "ሰይጣናት ናቸው!" የሚለው ሓሳዊና እኩይ፡ ነገረ-ጽሕፈት ነው።

Pages